አዲሱን የ፮ኛ ፖትርያሪክ ምርጫ እቃወማለሁ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ነጻነቷን ካገኘችበት ከዛሬ 60 ዓመታት ጀምሮ የራሷን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሁም ፖትርያሪክ እየሾመች (እየቀባች) ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ አምስት ፖትርያሪኮችን ሾማለች በርካታ ኤጲስ ቆጶሳትን እና ሊቃነ ጳጳሳትን ሾማለች። ነገር ግን ፭ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፖትርያሪክ ህልፈት በኃላ የተነሳው ችግር ቤተክርስቲያኒቱ ከአሁን በፊት ገጥሟት በማያውቀው መልኩ ችግሩ የቤተክርስቲያናቱን ካህናት፣ እና ምዕመናን ማለያየት ጀምሯል። ለዚህም አይነተኛ ምክንያት እየሆነ ያለው በኢትዮጵያ ያለው ሃገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዛሬ ፳፩ በፊት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕልውናዋን እንድታጣ፣ ምዕመኗ እርስ በእርሳቸው እንዲለያዩ እና እንዳይተማመኑ በማድረግ፣ በቀጥታ የመንግሥት ካድሬዎችን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በማስገባት፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ በማስነሳት፣ በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ ካባ የለበሱ የፖለቲካ ሰዎች በማስገባት እና በመሳሰሉት ውዝግቦችን በመፍጠር የቤተክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ አቋም እና ህልውና ሲፈታተን እንደቆየ ሁሉም ምዕመን ወይንም ካህናት አባቶች በተጨባጭ መረጃዎች እና ቀጥተኛ በሆነ ጣልቃ ገብነት፣ ጳጳሳትን በማስፈራራት፣ የገዳማት ህልውናን በመድፈር፣ ይዞታዎቿን ለባለሃብት በመስጠት ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ትልቅ ፈተና ላይ ወድቋል።
ለዚህም ይመስላል በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መንግሥት ሃይሉን በማጠናከር የመንግሥት ደጋፊ ይልቁንም ለመንግሥት የቀረበ የአንድ ጎጥ ወይም ተወላጅ የሆነ ፮ኛ ፖትርያሪክ ለማስመረጥ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን) በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን እና ካህናት ከምርጫው በፊት እርቅ ይቅደም በማለት ተደጋጋሚ ተማጽኖ ቢያቀርቡም ‘ጆሮ ዳባ’ በሚል ይመስላል በኢትዮጵያ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም በተለያየ ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል የእርቀ ሰላሙን ሂደት ወደ ጎን በማለት ለ፮ኛው ፖትርያሪክ ምርጫ ለማድረግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል።
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታች
፩/ የኢትዮጵያ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን
፪/ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከምርጫው በፊት እርቀ ሰላም ይቅደም የሚለውን ትተው የሚመርጡት አባት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት ሊሆን
አይችልም
፫/ ከመንግሥት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሚያደርጉትን አባቶች አዝነንባችኋል
፬/ ቤተክርስቲያን ለሚደርስባት የበለጠ መለያየት እና መከፋፈል ምክንያት የሆኑትን አባቶች ታሪክ ሲወቅሳቸው ይኖራል
፭/ በሁሉም ወገን የሚገኙት አባቶች አሁንም ተደጋጋሚ ስህተት ከመስራት በተቻለ መጠን እንዲቆጠቡ እንማጸናለን
፮/ በአጠቃላይ በዚህ ዘመን የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በዘመናችን እየደረሰ ያለውን
መጠነ ሰፊ የሆነ ችግር አይተን እና ሰምተን በዝምታ ማለፍ በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አያድንም
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ከተራ ቁጥር ፩ እስከ ፮ ያሉትን ሃሳቦች እደግፋለሁ በቤተክርስቲያናችን ላይ እየተደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት እቃወማለሁ፣ የሚመረጠውም ፮ኛ ፖትርያሪክ እኛን ሊወክለን አይችልም ለምርጫው የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት እና እርብርብ አጥብቄ እቃወማለሁ፥ ተቃውሞዪንም ይሄንን ፒቲሽን በመፈረም አረጋግጣለሁ።
Comment