Peace and Unity for Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“በትሕትና፡ዅሉና፡በየዋህነት፡በትዕግሥትም፤ርስ፡በርሳችኹ፡በፍቅር፡ታገሡ፤
በሰላም፡ማሰሪያ፡የመንፈስን፡አንድነት፡ለመጠበቅ፡ትጉ።” ኤፌ 4:2-3
ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ዋሽንግተን ዲሲ
ለብጹዕ አቡነ ናትናኤል
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ
ለብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
በያላችሁበት:
ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስ : ብጹዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል እና ብጹዓን አባቶች
ቡራኬያችሁ ይድረሰን !
ጉዳዩ : በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያለውን ልዩነት አስወግዶ ሰላምና አንድነትን ስለማምጣት
እኛ ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረ በተለያዩ ስፍራዎች የምንኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባላት የሆንን ካህናት፡ ዲያቆናት፡ የሰንበት ት/ቤት አባላት፡ ማኅበራትና በጠቅላላው ማኅበረ ምዕመናን በፓትርያርክ ሲመት ምክንያት ይህች ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ በሃይማኖትና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በአስተዳደር ከሁለት በላይ መከፈሏ እጅግ ያሳስበናል:: ያሳዝነናልም:: ይኸው መለያየት ሀገሪቱን: ቤተክርስቲያኒቱንና ምዕመናኑን ከባድ ችግር ላይ መጣሉ ይታወቃል:: በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጡት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉትና መፍትሔ የሚገኝላቸው ፤ ዕርቀ-ሰላም ወርዶ፤ በፍቅር፤ በሕብረት፤ ተቀናጅተን ስንሠራ በመሆኑ አባቶቻችን ከሁሉ በፊት ለሰላምና አንድነታችን ቅድሚያ እንድትሰጡልን፤ ይህን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ላይ እየተጻፈ ያለውን መጥፎ ታሪክ የሚቀይር ፤ ተስፋ ለቆረጡ ምዕመናንና ምዕመናት የሚያጽናና ታላቅ ገድል እንድትሠሩልን እንለምናለን::
በመጨረሻም አባቶቻችን በሰውና በእግዚአብሔርም ፊት የሚከበሩበትን እርቀ ሰላምና አስተዳደራዊ አንድነትን በማምጣት አንድ ሃይማኖት፣ አንድ መንበር፣ አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ( ማለትም አንድ እረኛ አንድ መንጋ) እንዲኖረን የሚቻለውን ሁሉ እንድታደርጉ ስለኛ ኃጢአት በመስቀል ላይ ደሙን ባፈሰሰላት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምላክ እና በእናቱ በወላዲተ አምላክ ስም እንማጸናለን።
የአባቶቻችን አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነትን፤ ለሀገራችን ዕድገትና ብልጽግናን ያድልልን!
ማሳሰቢያ: የዚህ ፊርማ ማሰባሰቢያ ዓላማው አባቶችን መማጸን ብቻ ነው:: ከገንዘብ ጋራ የተያያዘ ምንም ነገር የለውም::
Comment